በሸገር ከተማ ቡራዩ ክ/ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ አደጋ 13 ሱቆች ወደሙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸገር ከተማ ቡራዩ ክፍለ ከተማ ጸራ ጽዮን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በንግድ ሱቆች ላይ የተከሰተው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
በእሳት አደጋው የተለያየ የንግድ ስራ የሚከናወንባቸው 13 ሱቆች መቃጠላቸውን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር አራት የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪ 30 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የተሰማሩ ሲሆን÷ የእሳት አደጋው ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቁመዋል፡፡
የእሳት አደጋው በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለማድረሱን ጠቁመው÷ አደጋውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር 1 ሰዓት ከ24 ደቂቃ መፍጀቱን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩልም ምሽት 5 ሰዓት አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 5 አየር ጤና አካባቢ በአንድ ግሮሰሪ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ