የምክር ቤት አባሉ ለተወከሉበት ምርጫ ክልል የ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ7 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ተረፈ ታደሰ በተወከሉበት ምርጫ ክልል ለሚገኝ ሆስፒታል የ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ አደረጉ።
በድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንች ወረዳ ተመራጭ የሆኑት አቶ ተረፈ በአካባቢው ለሚገኘው ሲዝ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ድጋፉን አስረክበዋል።
ሆስፒታሉ ማሽኖች እንዲሟሉለት ሲጠይቅ እንደነበር ጠቅሰው፤ ሁሉንም ነገር ከመንግስት ብቻ መጠበቅ ተገቢ እንዳልሆነና ማህበረሰቡ የሚችለውን ማበርከት እንዳለበት አመልክተዋል።
ዛሬ ያደረኩት ድጋፍ ላይ ሌሎች ሲጨምሩበት ሆስፒታሉን ሙሉ ያደርጋዋል ብለዋል፡፡
አቶ ተረፈ የምክር ቤት አባል ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሁለት አመታት በገጠር ቀበሌዎች ሶስት የምንጭ ውሃ አስገንብተው ለማህበረሰቡ ማስረከባቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።