በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር በመላ ሃገሪቱ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር በመላ ሃገሪቱ እየተካሄደ ነው።
መርሐ ግብሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመርሐ ግብሩ ላይ አሻራቸውን አኑረዋል።
በክልሎችም የየክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ ነዋሪዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት መርሐ ግብሩ እየተካሄደ ነው።
እስከ ምሽት 12 ሰአት ድረስ በሚቆየው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 9 ሺህ 500 ቦታዎች ካርታ (ጂኦስፓሻል ማፕ) እንደተዘጋጀላቸው ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በሁለተኛው ምዕራፍ (ከ2015 እስከ 2018 ዓ.ም) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 25 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል አቅዳ እየሠራች ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁለተኛውን ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ሰኔ 1ቀን 2015 ዓ.ም በአፋር ክልል ማስጀመራቸው ይታወሳል።
በአጠቃላይ የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር እንደየአካባቢው ሥነ-ምኅዳራዊ ሁኔታ ቢወሰንም እስከ መስከረም 2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚዘልቅ ተጠቅሷል።