የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና የእስያ አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና የእስያ አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ እና የእስያ አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጂዲ ሲንግ (ዶ/ር) ተፈራርመዋል፡፡
አቶ አክሊሉ ታደሰ የመግባቢያ ስምምነቱ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የእስያ አፍሪካ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እንዲሁም ወዳጅነትን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የእስያ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የእስያ አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጂዲ ሲንግ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷በኢትዮጵያ በተገነቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች መዋዕለ ንዋያቸውን ካፈሰሱ ባለሃብቶች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት የእስያ ባለሃብቶች መሆናቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡