ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ደኅንነትን በማስጠበቅ በአፍሪካ ተምሳሌት እንደምትሆን ተመለከተ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ደኅንነትን በማስጠበቅ ረገድ እያከናወነች ያለው ሥራ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ነው ሲል የአሜሪካ ትራንስፖርት ደኅንነት መስሪያ ቤት ገለጸ፡፡
መስሪያ ቤቱ ከሐምሌ 10 እስከ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ደኅንነት ልዩ የኦዲትና የፍተሻ ሥራ አካሂዷል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ደኅንነትን በማስጠበቅ በአፍሪካ ተምሳሌት እንደምትሆን ነው ያረጋገጠው፡፡
የሲቪል አቪየሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ የቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ያከናወናቸው የሪፎርም ትግበራ ሥራዎች ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ደኅንነቱን በማስጠበቅ በኩል አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተጠቅሷል፡፡
ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያው ምንም አይነት የሴኪዩሪቲ ክፍተት ችግር ግኝት ሳይኖር አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን መስሪያ ቤቱ ተመልክቷል።
በብሔራዊ መረጃና ደንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አስራት ቀጀላ÷ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፉ የተገኘው ውጤት በቀጣይ ይበልጥ ተነሳሽነትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተወዳዳሪነትና ተመራጭነት ማሳደጉንም ነው የተቀሱት፡፡
የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፉ ሰጠው ልዩ ትኩረት ለስኬቱ መገኘት ከፍተኛ ድርሻ አለው ነው የተባለው፡፡
በለዘብነትም÷ የሪፎርም ትግበራ ሥራዎች፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ዝርጋታ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርና በመቀናጀት ያከናወናቸው የደኅንነት ቁጥጥርና የፍተሻ ሥራዎች ለስኬቱ መገኘት ተጠቅሰዋል፡፡