የኮንዶሚኒዬም ቤትን ያለአግባብ ሰብረው በመግባት የተከሰሱ የፖሊስ አባላት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮዬ ፌጬ ኮንዶሚኒዬም ቤትን ያለአግባብ ሰብረው በመግባት የተከሰሱ ሁለት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በዕስራትና በገንዘብ ተቀጡ።
የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የሸገር ከተማ አስተዳደር የኮዬ ፌጬ ክፍለ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው።
የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት የሆኑት ሳጅን ኦላና ሙስጠፋ እና ሳጅን ሀሰን ሁምዳ ናቸው።
የሸገር ከተማ የኮዬ ፌጬ ክፍለ ከተማ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ በሕዳር ወር 2015 ዓ.ም ግለሰብ ያልገባባቸው ኮንዶሚኒዬም ቤቶችን በራሳቸው በሕገወጥ መንገድ ሰብረው መግባታቸው በተደረገ ቆጠራ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው በክሱ ተገልጿል።
በዚህም መሰረት ተከሳሾቹ የመንግስት ቤቶችን በሕገወጥ መንገድ በመያዝ የቤቶች ልማት አስተዳደርና ማስተላለፍ አዋጅ ቁጥር 231/2013 አንቀጽ 69 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 86 ንዕስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌን በመተላለፍ ክስ ቀርቦባቸዋል።
ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረበውን ማስረጃ የመረመረው የወረዳ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት በነበረ የችሎት ቀጠሮ ወንጀሉን መፈጸማቸው መረጋገጡን ገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።
በዚህም መሰረት እያንዳንዳቸው በስድት ወራት እስራትና በሁለት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ