Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በልማት ዘርፎች ለመሥራት መከሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የተመራው ልዑክ በሮም ጣሊያን በግሉ ዘርፍ ተሰማርተው ከሚሠሩ የንግድ ማኅበራት ጋር ሥኬታማ የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸው ተገለጸ፡፡

የንግድ ማኅበራቱ በአፍሪካ ፣ በሜዲትራኒያን እና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ላይ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

በውይይታቸው ወቅት ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና ጣሊያን በምጣኔ-ሐብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስትር መሥሪያ ቤታቸው ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

የጣሊያን ባለሐብቶች በኢትዮጵያ ቁልፍ በሆኑ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱም አበረታተዋል፡፡

በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ ተሠማርተው የሚገኙ ኢጣሊያን ባለሐብቶች እና ማኅበራት በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጅ (አይሲቲ)፣ በግብርና፣ በምግብ ማቀነባበሪያ እንዲሁም በማዕድንና ቱሪዝም ዘርፎች ላይ ቢሠማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

የ”ኮንፊንዴስትሪያል አሳፍሪካ ኤንድ ሜዲትራኖ” ዋና ዳይሬክተር ሌቲዚያ ፒዚ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡

በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሃምቢሳ የማኅበሩ አመራሮች ላሳዩት በኢትዮጵያ የመሥራት ፍላጎት ምስጋናቸውን አቅርበው ኤምባሲው በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም በሮም ከጣሊያን ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.