በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ 99 ሺህ 240 ዶላር ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ 99 ሺህ 240 የአሜሪካን ዶላር በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መያዙን የፌደራል ፖሊስ ገለፀ።
የፌደራል ፖሊስ እንደገለጸው÷ዶላሩ ሊያዝ የቻለው ሁለት ተጠርጣሪዎች 99 ሺህ 240 ዶላር ወደ ብር ሲቀየር 5 ሚሊየን 427 ሺህ 436 ብር በሻንጣ ደብቀው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ቱርክ ኢስታንቡል ሊያወጡ ሲሉ ነው፡፡
የፌደራል ፖሊስ፣ የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የጉምሩክ ኮሚሽን እንዲሁም የአየር መንገድ የሴኩሪቲ ሠራተኞች ሐምሌ 14 እና 15 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄዱት ጠንካራ ፍተሻ ተጠርጣሪዎቹን ከነ-ኤግዚብቱ በቁጥጥር ሥር አውለው ምርመራ እየተካሄደያ እንደሚገኝ የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
በመሰል የወንጀል ድርጊቶች የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በየትኛውም መንገድ ከሕግ ማምለጥ እንዳይችሉ የፀጥታ አካላቱ እየወሰዱ ያሉትን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።