400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙ ተገለጸ፡፡
መነሻውን ከጅቡቲ ወደብ አድርጎ መዳረሻውን ወረታ ከተማ ለማድረግ የተንቀሳቀሰው 400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያውን የጫነው ተሳቢ ተሽከርካሪ ከታሰበው ቦታ ሳይደርስ መያዙ ተገልጿል፡፡
የመኪናው አሽከርካሪ ከግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ህገ ወጥ ተግባሩን ሲሰራ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
ህገ-ወጥ ድርጊቱ የተፈፀመው በትናንትናው ዕለት በባሕርዳር ከተማ ሰባታሚት ቀበሌ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ከ140 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለግለሰቦች በህገ ወጥ መንገድ ቀደም ብሎ መሰራጨቱም ተገልጿል፡፡
ፖሊስ ባደረገው የቤት ለቤት ፍተሻም ከተሽከርካሪው ተራግፎ በግለሰቦች ቤት የተከዘነ በርካታ የአፈር ማዳበሪያ መገኘቱ ተመላክቷል።
89 ኩንታል ማዳበሪያ በአንድ ግለሰብ ቤት ተከዝኖ የተገኘ ሲሆን ሌላ ተጨማሪ 24 ኩንታል ማዳበሪያም ከሌላ ግለሰብ ቤት ተከዝኖ ተገኝቷል ነው የተባለው።
አሽከርካሪው በህግ ቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተደረገ ሲሆን፥ ህብረተሰቡ እንደዚህ ዓይነት ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በቀጣይ እንዲያወግዝ ተጠይቋል፡፡