በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘግይተው ለሚዘሩ ሰብሎች ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ ተጠየቀ
አዳስ አበባ ፣ ሐምሌ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘግይተው ለሚዘሩ ሰብሎች ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ተጠየቀ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ባበክር ሃሊፋ እንደገለጹት፥ ለ2015/2016 ምርት ዘመን ወደ ክልሉ የገባው የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት ሒደት ተጠናቋል።
የሥርጭት ሒደቱም ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች መከናወኑን ነው የጠቆሙት።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ሕገ ወጥ አካላት ከአፈር ማዳበሪያ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አንስተዋል።
በተመሳሳይ ለክልሉ የቀረበው የዩሪያ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ሙሉ በሙሉ መሠራጨቱን ተናግረዋል።
አሁን ላይም በክልሉ ዘግይተው ለሚዘሩ ሰብሎች ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ማስፈለጉን ገልጸዋል።
በዚህ መሠረትም ቢሮው ለግብርና ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በመላኩ ገድፍ