Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ህግን ለማስከበር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ህዝቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያሳይ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀጥታ አካላት በክልሉ ህግን ለማስከበር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ህዝቡ ድጋፍ በማድረግ የተለመደ ትብብሩን እንዲያሳይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በመግለጫቸው ላይ እንዳሉት÷ ህግ የማስከበር ሥራ የመንግስት ሃላፊነት ነው።

በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ሰላማዊውን ህዝብ በማወክና መንገድ በመዝጋት ችግር የሚፈጥሩ አካላት የክልሉን ልማትና የህዝቡን አንድነት እየጎዱ በመሆናቸው ከእዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ህግን ለማስከበር ወደ ተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ የሚደረግ ትንኮሳ መቆም እንዳለበት የገለጹት ይልቃል (ዶ/ር)÷ መላው የክልሉ ህዝብም ለሠራዊቱ ድጋፍ በማድረግ የተለመደ ትብብሩን እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ የሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች ልጅ የሆነውን የመከካከያ ሠራዊት ስም ማጥፋት ተገቢነት የሌለው መሆኑን መላው ህዝብ ሊገነዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

“የሀገር መከላከያ ሠራዊት የአገር ሉአላዊነትን የሚያስጠብቅ የህዝብ መከታ ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የሠራዊቱን እንቅስቃሴ ለመገደብ የሚደረጉ ጥረቶች መቆም አለባቸው ብለዋል።

በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለው ችግር ከመባባሱ በፊት ነፍጥ ማንገብ መቆም አለበት ነው ያሉት፡፡

በየአካባቢው በሚካሄዱ የውይይት መድረኮች በመሳተፍ ሀሳብን መሞገትና ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ ማስገንዘባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የክልሉ መንግስት ከዚህ ቀደምም ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው÷ አሁንም ሰላምን ለማጠናከር በየአካባቢው ከህዝቡ ጋር እየተወያየ መሆኑን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.