Fana: At a Speed of Life!

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን 6 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኝ ተተክሏል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመትከል ከታቀደው 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ እስካሁን ከ6 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኝ  መተከሉን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ እያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ እስካሁን ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 450 ሚሊየን የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎች ናቸው።

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስከ ፊታችን ነሐሴ 30 ቀን እንደሚቀጥል ጠቅሰው÷በቀሩት ቀናት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የተተከሉ ችግኞችን የፅድቀት ምጣኔ ወደ 90 በመቶ ከፍ ለማድረግ ይሰራል ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው÷ ወጣቶችን ማደራጀት ጨምሮ ለየተቋማቱ ሃላፊነት ለመስጠት የተዘረጉ አሰራሮች እንዳሉ ተናግረዋል።

ወጣቶችን በማህበራት በማደራጀት በተፋሰስ አካባቢ የተተከሉ ችግኞን እንዲንከባከቡ ሃላፊነት መሰጠቱንም አስረድተዋል፡፡

ተቋማት የተከሉትን ችግኝ እንዲንከባከቡ እና የፅድቀት ምጣኔን ከፍ እንዲያደርጉ  ውል እንዲፈፅሙ ተደርጓልም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው፡፡

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም እስካሁን 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሔክታር መሬት በችግኝ መሸፈኑን ጠቁመዋል፡፡

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.