ከግማሽ ሚሊየን በላይ የመዲናዋ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተመረቁ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
የውኃ ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን ዕለታዊ የውኃ ምርት እና ስርጭት እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገድ አቅም ከፍ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል፡፡
ፕሮጀክቶቱ እስከ 500 ሜትር ጥልቀት ያላቸው፣ በቀን 67 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውኃ መስጠት የሚችሉ 25 የውኃ ጉድጓዶች ቁፋሮ እና የውኃ መሠረተ ልማት ግንባታን ያካተተ ነው ተብሏል።
የውኃ ጉድጓዶቹ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች፣ 31 ኪሎ ሜትር የተለያዩ ስፋት ያላቸው የውኃ መስመር ዝርጋታ እና እስከ 1 ሺህ 500 ሜትር ኪዩብ የመያዝ አቅም ያላቸው የማጠራቀሚያ ጋን ሥራ የተከናወናላቸው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም የከተማዋን ዕለታዊ ውኃ የማምረት አቅም ወደ 792 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ከፍ ማረግ እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡
ለጋራ መኖሪያ ቤቶች 138 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ እና 40 ኪሎ ሜትር የተለያዩ መጠን ያላቸው የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታም ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።