Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ በመኸር ወቅት በ45 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ ለማልማት ታቅዷል

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በመኸር ወቅት በ45 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ ለማልማት መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ የግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ እና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በክልሉ የሩዝ ሰብል በስፋት አይለማም ነበር።

ለአብነትም ባለፈው ዓመት የመኸር ወቅት 4 ሺህ 575 ሄክታር መሬት ላይ የሩዝ ምርት ለምቶ 178 ሺህ269 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም በዘንድሮው መኸር በ10 እጥፍ በማሳደግ በ45 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በማልማት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የሩዝ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል፡፡

ይህም በክልሉ በመኸር ወቅት በአጠቃላይ ለማልማት ከታቀደው 323 ሺህ 294 ሄክታር መሬት ውስጥ እንደማይካተት ገልጸዋል።

እስካሁንም 4 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመው፤ ማሳን በዘር የመሸፈን ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው አቶ አሸናፊ ያመላከቱት፡፡

የክልሉ ሩዝ የማልማት አቅም እስከ 125 ሺህ እንደሚደርስ ገልጸው፤ የዘር አቅርቦች ችግር ባለው አቅም ልክ ማልማት እንዳይቻል እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል።

ችግሩ ምርታማነታቸው ያልተረጋገጡ ዘሮችን አርሶ አደሩ እንዲዘራ ያስገደደ መሆኑንም አመልክተው፤ በምርት ሂደቱ የአፈር ማዳበሪያ እና የዝናብ መቆራረጥ ሌላው እንደችግር የሚነሳ መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡

የዘር አቅርቦት ችግሩን ለመፍታትም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡

ምርቱ በክልሉ በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ፣ በካፋ ዞን ጊንቦና ጎባ ወረዳዎች፣ በሸካ ዞን የኪ ወረዳ፣ በኮንታ ዞን ኮይሻ እና ኤላ ወረዳዎች፣ በዳውሮ ዞን ተርጫ ዙሪያ ወረዳ እንዲሁም በምዕራብ ኦሞ ዞን ሁሉም ወረዳዎች እየለማ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.