Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ-ህንድ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ህንድ ከሁለት ሺህ ዓመታት የተሻገረ ሁለንተናዊ ግንኙነት እንደነበራቸው የተለያዩ መዛግብት ያስረዳሉ።

ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮም በርካታ የህንድ ተወላጆች ኢትዮጵያን የኑሮ ምርጫቸው እንዳደረጉ የሚያመለክቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ።

በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መካከል በነበሩት ዓመታት በርከት ያሉ ሕንዳውያን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡

በፈረንጆቹ 1948 ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረተች ሲሆን በአምባሳደር ደረጃ ግንኙነታቸውን ያሳደጉትም በፈረንጆቹ ከ1952 ጀምሮ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በወቅቱ በርካታ ህንዳውያን መምህራን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በየጠቅላይ ግዛቱ ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በማስተማር ላይ ቆይተዋል።

ከሁለት ትውልድ በላይ የተሻገረው የሀገራቱ የትምህርት ዘርፍ ትብብር የኢትዮጵያን የከፍተኛ ትምህርት አቅም ለማሳደግ ያስቻለ ሲሆን፤ በርካታ ኢትዮጵያውያንም በህንድ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ እንዲያገኙ በማድረግ የተማረ የሰው ሃይል በማሟላት በኩል ሚናውን ተጫውቷል።

የብሔሮች፣ የሃይማኖቶች፣ የባህሎችና የመልክአ-ምድር ስብጥሮች ኢትዮጵያ እና ህሕድን እንደሚያመሳስላቸውና ያሉበት ጂኦፖለቲካዊ ቀጠና በፖለቲካ እና በውጭ ግንኙነት እንዲተባበሩ አስችሏቸዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ሀገራቱ ያላቸው ሁለንተናዊ የልማት ትብብር በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቀላል ብድር፣ የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ላይ በማተኮር እያደገ መጥቷል።

የኢትዮጵያ እና የህንድ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አገራቱ በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ መስክ ተጠቃሚ በማድረግ ላለፉት 74 ዓመታት ዘልቋል።

ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን በተለያየ አጋጣሚ ያረጋገጠችው ህንድ፤ ለረዥም ዘመናት የዘለቀው ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ አሁንም ቀጥሏል፡፡

ሀገራቱ በኢኮኖሚ ልማት፣ በንግድ ትስስር፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ሌሎችም መስኮች ጠንካራ ግንኙነት አላቸው፡፡

ህንድ በአዲስ አበባ የሚገኘውን ኤምባሲዋን በአዲስ መልክ በመገንባት ማስፋፋቷ የትብብር ግንኙነቱን ለማጠናከር ያላትን ፅኑ አቋም አሳይቷል።

ኢትዮጵያ እና ህንድ በልዩ ልዩ ወታደራዊ መስኮች በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ፈርመዋል።

ይህም በዘርፉ አቅም ግንባታ፣ በመከላከያ ጥናትና ምርምር፣ በመከላከያ ኢንዱስትሪዎች፣ በሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች በትብብር ለመስራት ከማስቻሉም በላይ የሀገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ያጠናከረ ነው።

ሀገራቱ ረጅም ዘመናትን የተሻገረ የዲፕሎማሲ ትብብር እና የንግድ ትስስራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ዘላቂ ኢኮኖሚ በመገንባት ብልጽግናን ለማረጋገጥ እያከናወነች ያለውን ሪፎርም በብሪክስ ማዕቀፍ ለማገዝ ህንድ ዝግጁ መሆኗንም ከዚህ ቀደም አረጋግጣለች፡፡

በልማት ስራዎች የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና በዕውቀትና ስትራቴጂ በትብብር በመስራት ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ ህንድ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.