Fana: At a Speed of Life!

ግብር የማይከፍሉ ነጋዴዎችን ወደ ግብር መረቡ ለማስገባት በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ መስራት ይገባል- ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብር የማይከፍሉ ነጋዴዎችን ወደ ግብር መረቡ ለማስገባት በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ መስራት ይገባል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡

የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉሙሩክ ኮሚሽን የ2015 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተገምግሟል፡፡

በበጀት ዓመቱ ኦዲት ከተደረጉ 7 ሺ 58 ግብር ከፋዮች ወለድ ፣ መቀጫና ፍሬ ግብርን ጨምሮ 40 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ እንደተናገሩት÷ የግብር ዘርፉን ለማሳደግና ሁሉም አካል ወደ ግብር መረቡ እንዲገባ በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በማገዝ ለማዘመንና ከፍተኛ ገቢ ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷በበጀት ዓመቱ ከ93 በመቶ በላይ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በኦንላይን ማሳወቃቸውን አንስተዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የገቢው ዘርፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተደራሽነቱን በማስፋት ከዘርፉ የሚጠበቀውን ገቢ ከፍ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው÷ ለዚህም በዘርፉ ያሉ መረጃዎችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ታክስን ማሳወቅ ላይ ያለውን መልካም አፈጻጸም በታክስ ክፍያ ላይም እውን ለማድረግ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የታክስ ዘርፉን ማስፋትና ወደ ታክስ መረቡ ያልገቡ ነጋዴዎችን ወደመረቡ በማስገባት ረገድ በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ መስራት ይጠበቃል ማለታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.