Fana: At a Speed of Life!

ሁሉም የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በከተማ ግብርና ስራ እየተሳተፉ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሁኑ ወቅት ሁሉም የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በከተማ ግብርና ስራ እየተሳተፉ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከተሞቻችን የገጠር ምርት ጠባቂዎች ከመሆን ተላቀው አምራቾች እንዲሆኑ መንግስታችን ግልፅና በጥናት ላይ የተመሰረተ ግብ እውን ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

የመንግስት የመጀመሪያው ስትራቴጂ ከተሞችን በቀጥታ ግብርና ስራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚሰራው ስራ ያላቸውን ሚና ማሳደግ እንደሆነም ገልጸዋል።

ይህንንም ለማሳካት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች በተሰራው የከተማ ግብርናን የማስተዋወቅ ስራ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ከተሞች በምርት እየተሳተፉ እንደሆነ አመልክተዋል።

የምርት ቁጥርና ዓይነትም በየዓመቱ እየጨመረ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በ2015 ዓ.ም የምርት ዘመን 35 ሺህ 286 ሄክታር መሬት በምግብ ሰብል በመሸፈን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።

በዚህም ከዕቅድ በላይ በማሳካት 42 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በማልማት 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ምርት ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

በአትክልት ምርት በበጋ እና በመስኖ 8 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ፣ ከእቅድ በላይ 11 ሺህ 79 ሄክታር መሬት በማልማት 1 ሚሊየን 739 ሺህ 849 የአትክልት ምርት ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ በከተሞች ያለውን መሬት፣ ሁሉንም የቴክኖሎጂ አማራጮች ተጠቅሞ በማልማትና ምርታማነትን በማሳደግ የከተማን የገጠር ምርት ጥገኝነት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.