አማካሪ ኮሚቴው ለምክር ቤቱ የቀረበውን የአስቸኳይ ጊዜ አጀንዳ አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምክር ቤቱ አማካሪ ኮሚቴ አጀንዳውን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።
በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 93 ንዑስ አንቀፅ 1 (ሀ) መሠረት ሐምሌ 29 ቀን 2015 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 መደንገጉ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካሪ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ የቀረበውን የአስቸኳይ ጊዜ አጀንዳ በተመለከተ የጉዳዩን አሳሳቢነት በጥልቀት አይቶና ተወያይቶ ለምክር ቤቱ ቀጣይ አስቸኳይ ጉባኤ እንዲቀርብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአጀንዳነት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መርምሮ ውሳኔ ለማሳለፍ ለአባላቱ አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
በዚሁ መሠረት ምክር ቤቱ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል፡፡
በመሆኑም የምክር ቤት አባላት በዕለቱ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በአካል በመገኘት ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ተላልፏል፡፡