ዩኒሴፍ በትግራይ ክልል ለሚካሄደው የክትባት ዘመቻ የ45 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ከነገ ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የክትባት ዘመቻ ይካሄዳል፡፡
የክትባት ዘመቻው “እንከተብ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን÷ከነሐሴ 9 እስከ ነሐሴ18 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡
በዘመቻው የኮቪድ-19 እና የማሕጸን ጫፍ ካንሰር ክትባት 14 ዓመት ለሆናቸው ሴቶች እንደሚሰጥ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶ/ር ሪእየ ኢሳያስ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በዘመቻው መደበኛ ክትባት ላልጀመሩ እና ላቋረጡ ዕድሜያቸው ከ2 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ክትባት ይሰጣል ተብሏል፡፡
ለክትባት ዘመቻው ስራ ማሰኬጃም የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ ) የ45 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን የደርጅቱ ተወካይ አቶ ያይንሸት ገ/ዮሃንስ ተናግረዋል፡፡
ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ተወካዩ÷ሕብረተሰቡ የክትባቱን ጠቀሜታ በመገንዘብ ህጻናትን እንዲያስከትብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡