በአማራ ክልል የባጃጅ ትራንስፖርት ክልከላ በተጣለባቸው ከተሞች አገልግሎቱ ነገ እንዲጀመር ዕዙ ፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ክልከላ በተጣለባቸው ስድስት ከተሞች ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጀምሩ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ፈቀደ።
ዕዙ በሰጠው ቁጥር ሁለት ወቅታዊ መረጃ ዛሬ ማለዳ ላይ ባደረገዉ ግምገማ የሁለተኛዉ ዙር ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሥራዎች ከሞላ ጎደል እየተጠናቀቁና እየተወሰደ ባለዉ ርምጃ አብዛኞቹ አካባቢዎች ወደ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሱ መሆናቸዉን አረጋግጧል፡፡
በሁሉም አካባቢዎች ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዉይይት መጀመሩን፣ የመንግሥት፣ የግልና የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ወደ መደበኛ ሥራቸዉ እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
ሕዝቡ ለመከላከያ ሠራዊታችን እያሳየ ያለው አቀባበል፣ የስንቅና የማበረታቻ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን፣ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ ያለው ፍላጎትና እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ዕዙ አረጋግጧል፡፡
አርሶ አደሩ ወደ መኸር አዝመራ ሥራዉ እየተመለሰ እንዲሁም የግብርና ግብአቶችን ወደየአካባቢዎቹ ለማጓጓዝ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ዕዙ ገምግሟል።
የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥብቅ መመሪያ የሰጠው ዕዙ፤ ክልከላ በተደረገባቸው ከተሞች የባጃጅ ተሸከርካሪዎች አገልግሎት እንዲጀምሩ ከኅብረተሰቡ የቀረበዉን ጥያቄ መርምሮ ከነገ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ፈቅዷል፡፡
ከዚህም ጋር በማያያዝ ክልከላዉ ከተነሣበት ጊዜ ጀምሮ የባጃጅ ባለቤቶችና አሽካርካሪዎች የጽንፈኛ ቡድኑን አባላት፣ የዘረፉትን ንብረቶችና የትኛዉንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ከማጓጓዝ እንዲቆጠቡና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ይህንን ተላልፈዉ በተገኙት ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማሕቀፍ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ መስጠቱን በመግለጫው አመልክቷል።