Fana: At a Speed of Life!

ኤምባሲው በኢትዮጵያና በአሜሪካ ምሁራን መካከል አጋርነትና ትብብር እንዲኖር እንደሚሰራ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያና በአሜሪካ ምሁራን መካከል ቀጣይነት ያለው አጋርነትና ትብብር እንዲኖር እንደሚሰራ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ገለጸ።

የአሜሪካ ኤምባሲ የአመራርና አስተዳደር አካል በሆነው የአቅም ግንባታ አውደ ጥናት ላይ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግሥት ጉዳይ ፈፃሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን፤ የኤምባሲው አመራርና አስተዳደር ሁለተኛ ቡድን ባዘጋጀው መክፈቻ ላይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

በዚህ መርሐ ግብር 19 የኢትዮጵያ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን በመወከል 25 ፕሬዚዳንቶች እና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች መሪዎች ሃሳብ እንደሚለዋወጡም ነው የተገለጸው።

በኦሃዮ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ ኢኒሼቲቭ የተዘጋጀው አውደ ጥናት ይህንን የተሳታፊዎች ቡድን ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ አሰባስቧል።

አምባሳደር ጃኮብሰን ተሳታፊዎቹ በየዩኒቨርሲቲዎቻቸው ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ያላቸው ቁርጠኝነት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ አቅም እውን ለማድረግ ቁልፍ እንደሆነም ነው ያነሱት።

አክለውም በኢትዮጵያውያን እና በአሜሪካ ምሁራን መካከል ቀጣይነት ያለው አጋርነትና ትብብር እንዲኖር የአሜሪካ ኤምባሲ እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡

በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ቡድኑ ለሁለት ሳምንታት በቴክሳስ ቴክ፣ በኦክላሆማ ግዛት እና በኦሃዮ ግዛት ዩኒቨርሲቲዎች ወደ አሜሪካ እንደሚጓዝም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች በአሜሪካ የትምህርት አመራርና አስተዳደር በመመርመር በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርትን አቅም ለማሳደግ ከባልደረቦቻቸውና ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር ተሞክሮዎችን ይለዋወጣሉ ተብሏል።

በውድድር ሂደት፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የአመራርና አስተዳደር መርሐ ግብር ሁለት ቡድኖችን መርጧል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ 19 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 25 ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች እና የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች በፈረንጆቹ 2022 ወደ አሜሪካ መጓዛቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ አስታውሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.