በኦሮሚያ ክልል ከ44 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሸፍኑ የግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ተከናውኗል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በሶስት ዞኖች ከ44 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሸፍኑ ሶስት የግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን በበጀት ዓመቱ መከናወኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በክልሉ በጉጂ ዞን በሰባ ቦሩ ወረዳ የሞርሞራ፣ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ የኤረር እንዲሁም የራሚስ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ቡርቃ ዲሚቱ ወረዳ በበጀት ዓመቱ ጥናትና ዲዛይናቸው የተከናወነ ፕሮጀክቶች ናቸው ተብሏል፡፡
የፕሮጀክቶቹ ጥናትና ዲዛይን ስራዎች የሚሸፍኑት ሄክታር 10 ሺህ፣ 4 ሺህ 150 እና 30 ሺህ ሄክታር በቅደም ተከተል የሞርሞራ፣ የኤረር እና የራሚስ መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡
የኤረርና ራሚስ የግድብና መስኖ ልማት የጥናትና ዲዛይን ፕሮጀክቶች ውል በሕዳር ወር 2015 ዓ.ም የተገባ ነው ተብሏል፡፡
የኤረር በ12 ወራት እንዲሁም የራሚስ በ16 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የኤረር የግድብና መስኖ ልማት የጥናትና ዲዛይን ፕሮጀክት ከመስኖ ልማት በተጨማሪ ለሐረር ከተማ የንፁሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦትም በጥናቱ እንደተካተተ ተገልጿል፡፡
የሞርሞራ የግድብና መስኖ ልማት የጥናትና ዲዛይን ፕሮጀክቶች ውል በጥር ወር 2015 ዓ.ም የተገባ ሲሆን÷ በ12 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል ተብሏል፡፡