Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ በመልካም ሁኔታ ላይ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላት በአዲስ አበባ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን እና በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጎብኝተዋል።

ተጠርጣሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ የሚገናኙበት፣ ከጠበቃዎቻቸው ጋር የሚማከሩበት እና የቃል መቀበያ ክፍሎችን በጉብኝታቸው ተመልክተዋል።

ጀከጉብኝቱ በኋላም ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግሥቴ ጋር ተወያይተዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ ከተጠርጣሪዎች ጋር ስላለው ሰብአዊ መብት አያያዝ ውይይት በማድረግ መረጃ መሰብሰባቸውን ገልጸው÷ ውይይቱ በተጠርጣሪዎቹ ፍላጎት መሰረት መገናኛ ብዙሃን በሌሉበት በዝግ መካሄዱን ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ መልካም መሆኑን፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ የሚገናኙበት ሁኔታ መኖሩን፣ ምቹ የማረፊያ ክፍሎች እንደተዘጋጁላቸው፣ የቃል መቀበያ ክፍሎች ንጹህና ሂደቱም በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑን በጉብኝታችን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ አካላዊ ሁኔታቸው ጤናማ መሆኑንና ሰብዓዊ መብት አያያዛቸው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተመልክተናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይ ተጠርጣሪዎቹ ምርመራቸው ተጠናቆ በፍጥነት ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው ከቢሮው ጋር መግባባት መደረሱን ጠቅሰዋል።

በማዕከል የተጀመረውን ተጠርጣሪዎችን የመጎብኘት ተግባር በቀጣይ በአማራ ክልልም እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ÷ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በአዲስ አበባና በአማራ ክልል በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር 226 መሆኑን ገልፀዋል።

ተጠርጣሪዎች ስለሚገኙበት ሁኔታና ሰብዓዊ መብት አያያዛቸው እንዲሁም የምርመራ ሂደቱን በሚመለከት ከቦርዱ ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የምርመራ ሂደቱን በማጠናቀቅ ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግና ተጠርጣሪዎችንም ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

መርማሪ ቦርዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ምክንያት በማድረግ ያልተገባ እስር በአዲስ አበባና ሌሎችም አካባቢዎች እየተፈጸመ ነው በሚል የሚነሳ መረጃ እንዳለ የጠቀሱት አቶ አዝመራው÷ ቦርዱ ክትትል አድርጎ መረጃውን ለህዝብ በይፋ እንደሚያሳውቅ አስረድተዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም በበኩላቸው÷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ህግን መሰረት አድርጎ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ብቻ በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በአዋጁ ስም የትኛውም አካል ሰዎችን ማንገላታትም ሆነ ለእስር መዳረግ እንደማይችልና ፈፅሞ በተገኘ አካል ላይም ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ ነው ያስገነዘቡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.