Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ለተሰጣት እውቅና የእንኳን ደስ ያለሽ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 54ኛው የዓለም አትሌቲክስ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ላበረከተችው አስተዋጽኦ ለተሰጣት የ”ፕላክ ኦፍ ሜሪት” እውቅና የእንኳን ደስ ያለሽ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንቷ በመልዕክታቸው÷ “ውድ ደራርቱ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአትሌቲክስ ላደረግሽው የላቀ አስተዋጽኦ ለተሰጠሽ እውቅና እንኳን ደስ አለሽ” ብለዋል።

“ለዚህ መብቃትሽ ለስፖርቱ ያለሽን የማያወላውል ቃል ኪዳን ለምናውቅ ሰዎች አልገረመንም፤ የበለጠም ይገባሻል፣ ሁሌም ለልባችን ደስታን ታመጫለሽ” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በተለይም በእጅጉ በሚያስፈልገን ጊዜ በፈረንጆቹ 1992 ታሪክ የሠራሽው ውድድሩን በድል አድራጊነት በማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ለተፎካካሪሽ ያሳየሽው የመንፈስ ከፍተኛነት፣ ማሸነፍ እንዳለው ሁሉ መሸነፍም እንዳለ፣ ለማሸነፍ ሕጉን ተከትሎ ለቀጣይ ውድድር መዘጋጀት ብቻ እንደሆነ ዓለምን አስተምረሻል ብለዋል፡፡

“ከስፖርትም አልፈሽ ከተራነት በላይ ከፍታን ሁሌም በመያዝ ለዚህች ለአንዷና ብቸኛ ሀገራችን ለምታደርጊው እናመሰግናለን” ሲሉም መግለጻቸውን የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ እድገት ላበረከተችው አስተዋፅኦ የ”ፕላክ ኦፍ ሜሪት” ሽልማትና እውቅና በቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ጉባዔ ላይ እንደተበረከተላት ይታወቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.