Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን በውድድር እንደሚቀበል ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ2016 የትምህርት ዘመን ጀምሮ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን በውድድር እንደሚቀበል አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሰረት የመጀመሪያው የመንግስት ራስ ገዝ አስተዳደር ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ይታወቃል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ የራስ ገዝ አስተዳደር ውሳኔው የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ እና የአስተዳደር ሙሉ ነፃነት ኖሮት በሃላፊነት እንደሚሰራ ነው ያረጋገጡት።

በዚህም ከ2016 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በትምህርት ሚኒስቴር የመቁረጫ ነጥብ ያገኙ የቅድመ ምርቃ ተማሪዎችን አወዳድሮ እንደሚቀበልም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝነትን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር የሚያስችሉ ከአስተዳደር መመሪያዎች ዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ ሰነዶችን ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

የጥናትና ምርምር ስራውን ለማሳለጥ የሚያግዙ የፋይናንስ፣ የሰው ሃይል አስተዳደር እና የግዥ መመሪያዎች እንደሚሻሻሉ መጥቀሳቸውንም የዩኒቨርሲቲው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.