Fana: At a Speed of Life!

በዘንድሮው ክረምት እስካሁን 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል – ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተፈራ ታደሰ÷ ባለፉት አራት ዓመታት ከተከናወኑ ሥራዎች ተሞክሮዎችን በመውሰድና ክፍተቶች በመሙላት ዘንድሮ ስኬታማ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

በዚህም በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በቂ የዝግጅት ሥራ በመሠራቱ÷ እስካለፈው ሣምንት ድረስ በተሰበሰበ መረጃ ከዕቅድ በላይ ስኬታማ ሥራ ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት፡፡

እስካሁን የተተከሉት ችግኞችም÷ የደን፣ ቀርከሃ፣ ዘርፈ ብዙ የጥምር ደን እርሻ፣ የፍራፍሬ፣ የመኖ እንዲሁም የሥነ ውበት ችግኞች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በሥራው ላይም በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች በንቃት መሳተፋቸውን ጠቅሰው÷ በ53 ነጥብ 3 ሚሊየን የሰው ቀናት (ምልልሶች) 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ነው ያረጋገጡት፡፡

ምንም እንኳን ሥራው ወደ መጠናቀቁ ቢሆንም÷ የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ መጠናቀቁ እስከሚገለጽ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

ሐምሌ 10 ቀን 2015 በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ÷ 566 ሚሊየን 971 ሺህ 600 ችግኞች በ302 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መተከላቸው ይታወሳል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.