Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የኮሌራ በሽታ እንዳይከሰት የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኮሌራ በሽታ እንዳይከሰት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ቦጋለ÷ በክልሉ አዋሳኝ በሆኑ አንዳንድ ቦታዎች የኮሌራ በሽታ በወረርሽን መልክ እየተከሰተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በሽታው ተላላፊ ከመሆኑ እና ከህብረተሰቡ ማህበራዊ ግንኙነት አንፃር በሽታው በክልሉ እንዳይከሰት እየተሰራ እንደሚገኝ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ያለውን የተጋላጭነት ስጋት መነሻ በማድረግ አሰሳ እና ቅኝት መደረጉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እስካሁን በክልሉ የኮሌራ በሽታ መከሰቱን የሚያሳይ ነገር እንደሌለ አረጋግጠዋል።

አሁንም ቢሆን ግን በሽታውን የመከላከል ስራዎች መቋረጥ የለባቸውም፤ ጠንካራ ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የኮሌራ በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች ውስጥ የተበከለ ውሃና ምግብ፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና ጉድለት፣ የመፀዳጃ ቤቶችን በአግባቡ አለመጠቀም ይጠቀሳል፡፡

እጅን በሳሙና እና በንፁህ ውሃ መታጠብ፣ ንፅህናው የተጠበቀ ውሃ መጠቀም፣ ምግብን በሚገባ ማብስልና ሳይቀዘቅዝ መጠቀም፣ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ንፅህናው በተጠበቀ ወይም በታከመ ውሃ አጥቦ መመገብ ከኮሌራ በሽታ መከላከያ መንገዶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.