በመዲናዋ በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ ነገ ይጀምራል- ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከነገ ጀምሮ በአዲስአበባ በምክክር ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን ልየታ ሊጀምር ነው።
ኮሚሽኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ፥ በተሳታፊዎች ልየታ ሂደት እገዛ የሚያደርጉ ተባባሪ አካላት መለየቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ም/ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የዕድሮች ማኅበራት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ እና የወረዳ አስተዳዳር በልየታ ሂደቱ እገዛ የሚያደርጉ ተባባሪ አካላት መሆናቸው በመግለጫው ተብራርቷል፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ በሰጡት መግለጫ÷ በመዲናዋ ባሉ ወረዳዎች የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ልየታ በሁለት የተለያዩ ምዕራፎች እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ በተሳታፊዎች ልየታ ሂደት እገዛ ለሚያደርጉ ተባባሪ አካላት ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታን በመምራትና በማስተባበር ውጤታማነቱን ይከታተላል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሀገራዊ ምክክሩ አመቺነት ሲባል በወረዳ ደረጃ የሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተለይተዋል ነው ያሉት።
በዚህም የሃይማኖትና የማሕበረሰብ መሪዎች፣ ሴቶች መምህራን፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ የግል ዘርፍ ተቀጣሪ ሠራተኞች፣ የንግድ ማሕበረሰብ አባሎች፣ ወጣቶች፣ ዕድሮች፣ በባህል እና በሙያቸው ምክንያት የተገለሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና ተፈናቃዮች (ባሉበት አካባቢ) ተሳታፊ እንዲሆኑ ተለይተዋል ብለዋል ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ።
በዙፋን ካሳሁን እና ምንይችል አዘዘው