11ኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሐ-ግብር ጳጉሜን 5 ቀን ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 11ኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሐ-ግብር ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት አስታወቀ።
ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በሚካሄደው የበጎ ሰው ሽልማት 27 ዕጩዎች ለመጨረሻ ዙር መቅረባቸው ተገልጿል።
ሽልማቱ በመምህርነት፣ ሳይንስ፣ ኪነ-ጥበብ፣ በጎ አድራጎት፣ ንግድ ኢንዱስትሪ እና ሥራ ፈጠራ፣ መንግሥታዊ ተቋማት ኃላፊነት፣ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ፣ሚዲያና ጋዜጠኝነት ፣ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ኢትዮጵያውያን በሚሉ 10 ዘርፎች ይካሄዳል ።
የዕጩዎች ጥቆማ ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ እስከ መጋቢት ወር 2015 ዓ.ም ድረስ በስልክ፣ በቫይበር፣ በቴሌግራም፣ በዋትስ- አፕ፣ በኢ-ሜይል እና በፖስታ እንደተደረገ ተመላክቷል፡፡
በዚህም ከመላ ኢትዮጵያ ከ200 በላይ ጠቋሚዎች እውቅና ማግኘት አለባቸው የሚሏቸውን 100 ያህል ግለሰቦች በ10 ዘርፎች ጠቁመዋል ።
እንደ 2014 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት ሁሉ ዘንድሮም ከ10 ዘርፎች መካከል በማህበራዊ ጥናት ዘርፍ በቂ ዕጩ ባለመገኘቱ በዘጠኝ ዘርፎች የሚሰጥ ሲሆን ዕጩዎች ተለይተዋል ።
በምንተስኖት ሙሉጌታ