የቻይና የመንገድ እና ድልድይ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መገንባቱን እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና የመንገድ እና ድልድይ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መገንባቱን እንደሚቀጥል የኮርፖሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ሊ ቻንጉይ አረጋገጡ፡፡
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከቻይና የመንገድ እና ድልድይ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ተፈራ ደርበው የኢትዮጵያን ከፍተኛ የመልማት ፍላጎት ያነሱ ሲሆን ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ቀጥሎ በመሠረተ ልማት ግንባታ እና በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፎች ላይ ቢሰማራ የሀገሪቷ ፍላጎት መሆኑን በውይይታቸው ወቅት አንስተውላቸዋል፡፡
አምባሳደሩ የቻይናው የመንገድ እና ድልድይ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ እያከናወናቸው ያሉትን በርካታ ፕሮጀክቶች ጠቅሰው አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
በቀጣይም በቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኮርፖሬሽኑን በሚያስፈልገው ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
የቻይናው የመንገድ እና ድልድይ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሊ ቻንጉይ በበኩላቸው ÷ በኢትዮጵያ ገንብተው ያጠናቀቋቸውን በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች አንስተዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከልም ኮርፖሬሽኑ የገነባቸው የቀለበት መንገድ ሥራዎች በጉልኅ የሚነሱ ናቸው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ከሚሳተፍባቸው ሥራዎች መካከል የታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ልማት እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ቅርንጫፍ ፅኅፈት ቤቶች እንዳሉት ጨምረው መናገራቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል፡፡
ቻይና እና ኢትዮጵያ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው ኮርፖሬሽኑም በሀገሪቷ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርበት መሥራቱን እንደሚቀጥል ነው ያሰመሩበት፡፡