የዓለም ባንክ ሥደተኞችን በተመለከተ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ ለሥደተኞች እና ሥደተኞችን ለሚያስተናግዱ ማኅበረሰቦች የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ እንዲያጠናክር የሥደተኞች እና ከሥደት ተመላሾች አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ጠይባ ሐሰን ጠየቁ፡፡
ዳይሬክተር ጀነራል ጠይባ ሐሰን ÷ በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ከፍተኛ ኦፊሰር ከሆኑት ሞሐመድ ከድር አብዴል-ራዚግ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ባንኩ በድጋፍ በኩል እስካሁን ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅዖም በመርሐ-ግብሩ ላይ ማመስገናቸው ተገልጿል፡፡
በቀጣይም አገልግሎቱ ይበልጥ የተሻለ ምላሽ ይሰጥ ዘንድ የዓለም ባንክ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ከፍተኛ ኦፊሰር ሞሐመድ ከድር አብዴል-ራዚግ በበኩላቸው ÷ የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ መንግስት እንዲሁም ከሥደተኞች እና ከሥደት ተመላሾች አገልግሎት ጋር በትብብር መሥራቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሥደተኞችን በማስተናገድ ረገድ እየተወጣች ያለውን ሚና አድንቀው የዓለም ባንክ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡