ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ ተደማጭነቷ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗ የኢኮኖሚ ትብብሮችን ከማስፋት ባለፈ በዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ተደማጭነቷ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ፡፡
በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬት የብሪክስ አዲስ አባል ሀገራት መሆናቸው ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 ሀገራት የብሪክስ አባል ለመሆን ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ የስድስት ሀገራት የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቅሰው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከጉባዔው ቀደም ብሎ ከብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እንዲሁም በኢኮኖሚው መስክ ያላትን መጻኢ ተስፋ በማሳየት በኩል ጉልህ ሚና አበርክተዋል ነው ያሉት፡፡
ይህም የኢትዮጵያ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ የኢኮኖሚ ትብብርና የኢንቨስትመንት አማራጯን እንደሚያሰፋም አምባሳደር ሬድዋን አብራርተዋል፡፡
የብሪክስ መጠናከር በአንድ የመገበያያ ገንዘብ የታጠረውን የዓለም ገበያ አማራጭ እንዲኖረው ዕድል እንደሚፈጥርም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይህም የልማት ፋይናንስ አማራጮችን በማስፋት ኢትዮጵያን ጨምሮ የታዳጊ ሀገራትን ተጠቃሚነት በማሻሻል በኩል ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ እያደገ በመጣው ብሪክስ አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተደማጭነት እንደሚያሰፋም ጠቁመዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው ÷ ባለፉት ጊዜያት በተሰሩ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎች በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያ ተደማጭነት እንዲሰፋ ማድረግ ማቻሉን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡