አምባሳደር ምሥጋኑ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ክሪስ ኒኮይ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አምባሳደር ምስጋኑ አስረድተዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ እንደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም ያሉ ተቋማት አጋዥነት መኖር ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡
የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ከአድሎዓዊ አሠራር በፀዳ መልኩ ተደራሽ እንዲሆን መንግስት ከሁሉም ግብረ-ሠናይ አካላት ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ክሪስ ኒኮይ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ለተጎዱ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
በውይይቱ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማገዝ እና በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡