በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፎችን ለማነቃቃት በትኩረት ይሰራል-ቢሮው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፎችን ለማነቃቃት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የክልሉ ኢንዱትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ቃሲም ኢብራሂም÷ባለፉት ዓመታት በነበሩት የፀጥታ ችግሮች የተቀዛቀዘውን የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ዘርፎች በ2016 የበለጠ ለማነቃቃት በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡
በክልሉ ዘርፈ-ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ የጠቀሱት ኃላፊው÷ እነዚህን ማጥናትና ማስተዋወቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢንቨስትመንት በዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለይቶ መፍትሔ ለመስጠት ያለመ እና ባለሃብቶችን ያሳተፈ የኢንቨስትመንት ፎረም እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡
በአሶሳ ከተማ ለሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የሚሆን 250 ሔክታር መሬት በመለየት ግንባታው እንዲጀመር ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚመረቱ ጥሬ ዕቃዎች በክልሉ ዕሴት ጨምረው ለሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል እንደሚሰራም አንስተዋል፡፡
በክልሉ በተለያዩ ከተሞች ለኢንዱስትሪ ክላስተር የሚውል 100 ሄክታር መሬት በክላስተር በማልማት የዘረፉን ልማት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡