“ኢትዮጵያ ለውጭ ንግድ የሚተርፍ ስንዴ እያመረተች ነው” – አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ትራንስፖርቴሽን
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለውጭ ንግድ የሚተርፍ ስንዴ እያመረተች መሆኗን አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ትራንስፖርቴሽን ገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ በተያዘው የምርት ዘመን ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የስንዴ ምርት ካለፈው ጋር ሲነጻጸር የ27 በመቶ ብልጫ እንደሚኖረው የግብርና ሚኒስቴርን መረጃ ጠቅሶ ጋዜጣው አመልክቷል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ÷ ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ምርት መቀነስ እና በሀገር ውስጥ ምርት መተካትን ማማከሉን አስታውሷል፡፡
ኢትዮጵያ በ2015 ስንዴ ወደ ሀገር ውስጥ አለማስገባቷን ጠቅሶ የሀገሪቱን ፖሊሲ ውጤታማነት አድንቋል፡፡
ስንዴ ባለማስገባቷም 1 ቢሊየን ዶላር ማዳኗን የግብርና ሚኒስትሩን ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ጠቅሶ አስነብቧል፡፡
ሚኒስትሩ በምርት ዘመኑ 19 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን የስንዴ ምርት እንደሚሰበሰብ መግለጻቸውን እና ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 15 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን የስንዴ ምርት ተሰብስቧል ማለታቸውን ጠቁሟል፡፡
የሀገሪቱ የስንዴ ምርት ፍጆታም 9 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን እንደነበር ነው ሚኒስትሩ ገልጸዋል ያለው ጋዜጣው፡፡
ኢትዮጵያ በመስኖና በዝናብ የምታመርተውን የስንዴ ምርት ለማሳደግ እንዲሁም÷ ከውጭ የምታስገባቸውን በሀገር ውስጥ መመረት የሚችሉ የግብርና ምርቶች ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለመተካት አቅዳ እየሠራች መሆኗን አመላክቷል፡፡
በተለይም ለቢራ ምርት ግብዓትነት የሚውለውን የማልት ገብስ በሀገር ውስጥ ለማምረት እንደሚሠራ የግብርና ሚኒስትሩን ጠቅሶ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ትራንስፖርቴሽን ዘግቧል፡፡