ርዕሳነ መስተዳድሮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለ2016 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ÷የምንቀበለው አዲሱ 2016 ዓ.ም የሀገራችንን ታላቅነት የምናረጋግጥበት እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የፖለቲካ ችግሮች መከማቸት፣ ድህነት፣ የመልካም አስተዳደርና የጸጥታ አለመረጋጋት ለልማት ጉዞ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
እነዚህ ፈተናዎች ቢኖሩም ኢትዮጵያን የአፍሪካ ብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተደረገው ጉዞ ስኬት ማስገኘቱን ጠቅሰዋል።
አዲሱ ዓመት በስራ ባህላችን መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ቃል የምንገባበት ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ስርዓት የምንገነባበትና የህዝባችንን ተጠቃሚነት የምናረጋግጥበት ወቅትም ነው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው የ2016 አዲስ ዓመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸው÷ በአዲሱ ዓመት የአብሮነትንና የበጎነትን መንፈስ በማፅናት በተለያየ የኑሮ ጫና ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግስት የሕዝብ አቅሞችን፣ የየአካባቢውን ፀጋዎችንና ሌሎችንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሞችንና እሴቶችን በማስተባበር አዳዲስ ለውጦችን ለማስመዝገብ ይሠራል ነው ያሉት ።
እንዲሁም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር) አዲሱን ዓመት አስመልክቶ መልዕክት ባስተላለፉት መልዕክት ዓመቱ በአዲስ መንፈስ፣ አስተሳሰብ፣ ህብረት፣ መተጋገዝ እና መደጋገፍ የበለጠ በመጠናከር ሀገራችንን ለመለወጥ የምንነሳበት ጊዜ እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል፡፡
አዲሱን ዓመትን ስናከብር ካለን በማካፋል፣ አቅመ ደካሞችን በመጠየቅና በኢትዮጵያዊ የመተባበርና የመተጋገዝ ባህል ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው÷በ2016 አዲስ ዓመት ሰላምን በማጠናከር የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሙሉ አቅም ይሰራል ብለዋል፡፡
አዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ የምንሰንቅበት፣ ለቀጣይ ስኬታችን የምናቅድበት፣ የመለወጥ፣ የመታደስና ይቅር በመባባል በጋራ የሚከበር በዓል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎችን በሙሉ አቅም መስራት እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ ዓመቱ ከፋፋይ አጀንዳዎች ተነቅለው አብሮነትና አንድነት የሚዳብርበት እንደሚሆንም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡