የልጆች የመጀመሪያዎቹ የትምህርት ቀናት ውሎና ከወላጆች የሚጠበቁ ተግባራት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማና በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ማስጀመሪያ ቀን ነው።
ታዲያ በዚህ ወቅት በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ የትምህርት ቤት ደጃፍን የሚረግጡ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት ሲገቡ የተለያዩ ባህሪዎችን ያሳያሉ፡፡
እንደ መምህራን ገለፃ በመጀመሪያዎቹ የትምህርት ቀናት ልጆች ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ስለሚመለከቱ ያለቅሳሉ፣ ወላጆቻቸውን አለቅም ብለው ያስቸግራሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ቶሎ ወደ መጫወቻ ስፍራ ይሮጣሉ፡፡
ለዚህም ወላጆች ልጆችን በስነልቦና ማዘጋጀት እና ቢቻል ቀደም ብሎ የትምህርት ቤቱን ነባራዊ ሁኔታ ማሳየት፣ በትምህርት ቤት ውስጥ እውቀት እንደሚቀስሙ እና ብዙ ጓደኞች እንደሚያፈሩ፣ እንደሚጫወቱ ቢነግሯቸው መልካም መሆኑን ይናገራሉ።
ይህን ማድረጉ ደግሞ ልጆች ጉጉት እንዲያድርባቸው ያደርጋል ነው የሚባለው፡፡
በሌላ በኩልም ብዙ ምሳ እቃ አስይዞ መላክ ትክክል እንዳልሆነ እና ልጆች በአቅማቸው የተመጣጠነ ምግብ (እንደ ወላጅ አቅም) እንዲመገቡ ማድረግ እንደሚገባም ነው የሚመክሩት፡፡
እንዲሁም የአመጋገብ ስርዓትን፣ የሽንት ቤት አጠቃቀምን፣ ልብስ አለባበስን እንዲሁም ደረጃ አወጣጥን ልጆች ተለማምደው ወደ ትምህርት ቤት ቢመጡ ስራዎችን ያቀላሉ ባይ ናቸው።
መምህራንም ተማሪዎችን በእድሜያቸው እና ስርዓተ ትምህርቱ ባስቀመጠው መሰረት በፍቅር፣ በጨዋታ ዕውቀትን ማስቀሰም እንዳለባቸው ይገልፃሉ፡፡
በፌቨን ቢሻው