ፕሬዚዳንት ፑቲን በቀጣዩ ወር ከቻይናው አቻቸው ጋር ሊመክሩ ነው
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 9 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቀጣዩ ወር በቻይና ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተሰማ።
የሩሲያ ብሄራዊ የፀጥታ ምክር ቤት ፀሃፊ ኒኮላይ ፓትሩሼቭ ፑቲን በቀጣዩ ወር ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በቤጂንግ እንደሚገናኙ ገልጸዋል።
ሁለቱ መሪዎች በቀጣዩ የፈረንጆች ወር በቻይና ሊካሄድ ቀጠሮ በተያዘለትና በዓለም አቀፍ ትብብር ላይ በሚመክረው የ’ቤልት ኤንድ ሮድ ጉባኤ’ ላይ ተገናኝተው ይወያያሉም ያሉት።
በውይይታቸውም በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው የተባለው።
የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ዋንግ ዪ ከዋና ፀሃፊው ጋር በሞስኮ ባደረጉት ውይይት፥ የሀገራቱ ግንኙነት በመከባበር መርህ፣ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ትብብር ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።
ፓትሩሼቭ አያይዘውም ሞስኮ በቻይና የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንደማትገባና እገዛ እንደምታደርግ መናገራቸውን አር ቲ አስነብቧል።
ዋንግ ዪ በበኩላቸው ሃገራቸው ለሀገራቱ የሁለትዮሽ አጋርነት እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላላቸው ለምታደርገው ድጋፍ ቁርጥኛ ናት ብለዋል።
ሩሲያ እና ቻይና ከቅርብ አመታት ወዲያ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያ መስኮች ያላቸው ትብብር እያደገ መምጣቱ ይነገራል።
በተለይም ሩሲያ ከምዕራባውያን ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን ተከትሎ ከቤጂንግ ጋር የምታደርገው ዘርፈ ብዙ ትብብር እየጎለበተ መምጣቱን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።