ከተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስኬታማ ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ውጤታማ ስራ እያከናወነች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ።
78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ “ሰላም፣ ብልጽግና፣ ለውጥና ዘላቂነት” በሚል መሪ ሐሳብ በኒውዮርክ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ልኡክ በመሳተፍ ላይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ባለፉት ሁለት ቀናት ከተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ባለስልጣናት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋር አካላት ተወካዮች ጋር ፍሬያማ ውይይቶችን አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
በዚህም በቀጣናው ሰላምን ለማጽናት የሚደረጉ ጥረቶች እንዲሁም በሁለትዮሸ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውይይቶች መደረጋችውን በማንሳትም፥ በዘላቂ ልማት ግቦች የመሪዎች የፖለቲካ ፎረም ላይ ኢትዮጵያ የልማት ግቦቹን በሚመለከት ያላትን አቋም እንዳስረዳችም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ባዘጋጇቸው መድረኮች ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መሳተፋቸውን አምባሳደር መለስ ተናግረዋል።
በመድረኮቹ ኢትዮጵያ ያሏትን ፍላጎቶች ለማሳወቅ እድል የፈጠሩ እንደነበሩም ጠቅሰዋል፡፡
የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ ከጉባኤው ጎን ለጎን የተመድና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ማሻሻያን አስመልክቶ ባዘጋጁት መደበኛ ያልሆነ ስብስባ ላይም የጸጥታው ምክር ቤት ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖረው አቶ ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል ነው ያሉት።
ከዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፎችን ማግኘት በምትችልባቸው ሁኔታዎች ላይ ስኬታማ ውይይቶች መደረጋቸውንም አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በ78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያና የመንግስታቸውን አቋም የሚገልጽ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።