የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ያላጠናቀቁ ተማሪዎችን ማስፈተን ጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ያላጠናቀቁ 11 ሺህ 581 የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ተማሪዎችን ተቀብሎ ዛሬ ማስፈተን መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሳሁን ተገኘ (ዶ/ር)÷ ባለፈው ጊዜ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር በዩኒቨርሲቲው ሲሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል ፈተና ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ፈተናውን ለመስጠት ተገቢው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ዛሬ በጠዋቱ የፈተና ክፍለ ጊዜ የኬሚስትሪ ፈተና በመስጠት ፈተናው መጀመሩን ገልጸዋል።
ከሰአት በኋላ ባለው ክፍለ ጊዜም ባዮሎጂ እንዲሁም ነገ ደግሞ የስነ ዜጋ ትምህርት በመስጠት የፈተና ሂደቱ እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል፡፡
የፈተና ሂደቱ ሰላማዊና ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ እየወሰዱ መሆናቸውን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዩኒቨርሲቲው 5 ካምፓሶች እየተሰጠ ባለው የፈተና ሂደት የዩኒቨርሲቲው መምህራን በፈታኝነትና በሱፐርቫይዘርነት ተመድበው ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።