በተለያዩ ክልሎች የ2016 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ክልሎች የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት በይፋ ተጀምሯል፡፡
በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የ2016 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደት በይፋ የተጀመረ ሲሆን÷ የክልሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች መርሐ ግብሩን አስጀምረዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው የቆዩ 53 ሺህ ሕጻናትን ጨምሮ በ2016 ዓ.ም 305 ሺህ 672 አዲስና መደበኛ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ ንቅናቄ ሲካሄድ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ እንዳስታወቀው፤ ዛሬ የመማር ማስተማር ሥራው የተጀመረው ቀደም ሲል ከመምህራን፣ ወላጆችና በየደረጃው ከሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር በተከናወነ ስራ ነው።
በጎርፍ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራው በሂደት እንደሚካሄድም ተጠቁሟል።
ወላጆች ከዛሬ ጀምሮ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ እንዲገኙ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጥሪ መቅረቡን የክልሎች ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደት በመጀመሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መሄድ እንዳለባቸው የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ አሳስቧል፡፡