ሴቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ያላቸው ሚና የሚጎለብትበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሴቶች በሀገራዊ ሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸው ሚና የሚጎለብትበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተጠየቀ።
በኦሮሞ ገዳ ስረዓት ያደጉና በገዛ ፍቃዳቸው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ሴት መሪዎች ዛሬ በአዳማ ከተማ በሀገራዊ የሰላም ሁኔታና የሴቶች ሚና ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከትምህርትና ምርምር ተቋማት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከወጣት ማህበራትና አደረጃጀት፣ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከሰላም እናቶች፣ ሃደ ሲቄዎች፤ ከሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ ናቸው።
ተሳታፊዎቹ ባደረጉት ምክክር በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሴቷ ተሳትፎ መጎልበት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በሀገራዊ ሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ በአጠቃላይ እና በኦሮሚያ ሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ በተለይ ሴቶች ያላቸው ውክልና ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው፤ የሰላም ግንባታ ሂደቶች ውስጥ ድምጻቸውን በጉልህ እንዳያሰሙ የሚያደናቅፉ መዋቅራዊ፣ ተቋማዊና ልማዳዊ ተግዳሮቶች መኖራቸውንም አመልክተዋል።
ሴት መሪዎቹ የኢሬቻ በዓልን እንደ ጥሩ እድል በመጠቀም የኦሮሞ ሴቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና እንዲያድግ ባስተላለፉት የሰላም ጥሪ፤ አለመግባባቶች በምክክርና በድርድር እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
በክልሎችና በሀገር አቀፍ ደረጃ ሽምግልና፣ ምክክርና ድርድርን ጨምሮ ሌሎች ዘላቂ የሰላም ግንባታ ሂደቶች ውስጥ የኦሮሞ ሴቶች ትርጉም ያለው ውክልና እንዲኖራቸው መደረግ እንዳለበት አንስተዋል፡፡
ሴቶች በግጭት ወቅትም ሆነ ከግጭት በኋላ ፆታን መሰረት ላደረጉ ጥቃቶች ስለሚዳረጉ፤ ይህም ከጦርነት በኋላ በሚደረጉ የሰላም ግንባታ ሂደቶች ውስጥ እንዳይሳተፉ ያደርጋቸዋል ሲሉም አንስተዋል።
ስለሆነም የሚመለከታችው አካላት በተለይም መንግስት ሴቶች በመሰል ሂደቶች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥር ነው የጠየቁት፡፡
ባለድርሻ አካላት ሴቶች ውሳኔ ማስተላለፍ ላይ በንቃተ እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ እና የሴቶች ሚና አስፈላጊነትን በሚመለከት ግንዛቤ እንዲፈጥሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ይህ የሰላም ሂደት እንዲሳካ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን ጉዳዩ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚሰሩ አካላት በጥምረት እንዲሰሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሀገር አቀፍ እና በክልሎች ደረጃ የሚደረጉ የሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ እንዲጎላ ከሚሰሩ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል፡፡