ምክር ቤቱ አምስት የብድር ስምምነት አዋጆችን አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓምት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው÷ ለተለያዩ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ የሚሆኑ አምስት የብድር ስምምነቶችን ለማጽደቅ የቀረቡ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ ልማት ማህበር መካከል ለኢትዮጵያ “ኤሌክትሪፊኬሽን” ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አዋጁን አጽድቋል፡፡
የብድር ስምምነቱ በፕሮጀክቱ አማካኝነት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ዜጎች የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ተደራሽነት እንዲጨምር ማድረግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በብድር ስምምነት የተገኘው 250 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ከወለድ ነጻ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ብድሩ የ6 ዓመት ችሮታን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ ልማት ማህበር መካከል ለሰው ሃብት ልማት “ኦፕሬሽን” ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን አዋጅ መርምሮ አጽድቋል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግስታት መካከል የቡናና ሻይ ባለስልጣን የኢትዮጵያ የቡና እሴት ሰንሰለት ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን አዋጅ መርምሮ አጽድቋል፡፡
በተመሳሳይ ም/ቤቱ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ፕሮጀክት የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጽድቋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ለውሃ እና ኢነርጂ ዘርፍ ለተቀናጀ የውሀ አስተዳደር ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን አዋጅም ምክር ቤቱ መርምሮ አጽድቋል፡፡
እንዲሁም ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደህንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር አዋጅ ለመደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሰው ሃብት ልማት ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ ቃለ ጉባዔን ማጽደቁ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ለህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽ ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን አዳምጧል፡፡
በየሻምበል ምሕረት