ስለድብርት (ድባቴ) ምን ያህል ያውቃሉ?
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ድብርት የአንድን ሰው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉል ብሎም ራስን እስከማጥፈፋት የሚያደርስ ስሜት ነው፡፡
ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ድብርት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይህም በዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴያቸው ላይ እንዲሁም የተለያዩ ግንኙነታቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በተጨማሪም አንዳንድ ሥር የሰደደ የጤና እክሎችን ሊያባብስ እንደሚችልም ነው የሚገለጸው፡፡ ለአብነትም – አስም፣ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች፣ ካንሰር፣ የስኳር በሽታ እንዲሁም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ይጠቀሳሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ የተስፋ መቁረጥ ስሜት የተለመደ የህይወት ክፍል ሲሆን፥ የሚያሳዝኑ እና የሚያበሳጩ ክስተቶች በሁሉም ሰው ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ስሜቶች ናቸው፡፡
ሆኖም ግን በመደበኛነት የጭንቀት ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ከተሰማዎት ለድብርት ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
ይህም ተገቢውን ሕክምና ሳያገኙ ከቀሩ ሊባባስ የሚችል ከባድ የጤና ችግር ሊያስከትልብዎ እንደሚችልም ሊገነዘቡ እንደሚገባ ኸልዝላይን በመረጃው ያመላክታል፡፡
ከፍተኛ ድብርት በስሜት ወይም በሰውነት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሲሆን፥ ምልክቶቹም በተከታታይ ሊከሰቱ ወይንም የሚመጡና የሚሄዱ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሀዘን፣ ጭንቀት ወይም የ”ባዶነት” ስሜት፣ ተስፋ ማጣት፣ ዋጋ ቢስነት ስሜት፣ ብዙ ማልቀስ፣ መረበሽ፣ መናደድ፣ ከዚህ ቀደም የሚያስደስትዎ ነገሮች ላይ ስሜት ማጣት፣ ድካም፣ የማተኮር (የማስታወስ)፣ የመወሰን ችግር፣ በዝግታ ማውራት (መንቀሳቀስ)፣ በቂ እንቅልፍ ያለማግኘት(መንቃት ካለብዎ ሰዓት በፊት መንቃት በወይም ከመጠን በላይ መተኛት)፣ የምግብ ፍላጎት ወይም የክብደት ለውጦች የድብርት ምልክቶች ናቸው።
በተጨማሪም ስለ ሞት፣ ራስን ማጥፋት፣ ራስን ስለመጉዳት ወይም ራስን የማጥፋት ሙከራዎች ማድረግ ከፍተኛ የድባቴ ወይም ድብርት ስሜት ውስጥ መሆንዎን ያመላክታል፡፡
የድብርት ምክንያቶች፡- የሆርሞን መለዋወጥ ወይም መዛባት፣ ዘር (የቤተሰብ ሁኔታ)፣ የልጅነት ጠባሳዎች፣ የጤና ሁኔታ፣ አልኮል ወይም እጾችን መጠቀም፣ ሕመም እና ሌሎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡
የድባቴ (ድብርት) ህክምናዎች፡- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ራስን መንከባከብ፣ መድሃኒት መውሰድ፣ ሳይኮቴራፒ ወይም ከሃኪምዎ ጋር ማውራት፣ ሜዲቴት ማድረግ ወይም ጽሞና፣ አኩፓንቸር (ባህላዊ የህክምና ዘዴ ሲሆን ይህን ከመጠቀምዎ በፊት ሃኪምዎን ያማክሩ)፣ ቪታሚኖችን መውሰድና የመሳሰሉት ናቸው፡፡