Fana: At a Speed of Life!

ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ተቀናጅቶ ለመከላከል የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት አባል ሀገራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ተቀናጅቶ ለመከላከል የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት አባል ሀገራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

25ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 14 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የብሄራዊ ኢንተርፖልና ዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደጀኔ በቀለ÷ 25ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በቡሩንዲ አስተናጋጅነት ቡጁምቡራ ጥቅምት 14 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት አባል ሀገራት ፖሊስ አዛዦችና ዓለም አቀፍ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ተወካዮች በጠቅላላ ጉባኤው ላይ እንደሚሳተፉ ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት የቋሚ አስተባባሪ ኮሚቴ እና በሥር ያሉ የህግ፣ ፀረ-ሽብር፣ የትምህርትና ስልጠና፣ የሥርአተ ጾታ፣ የሳይበር ደኅንነት የቴክኒካል ንዑስ ኮሚቴዎች በዛሬው ዕለት የጋራ ስብሰባና የተናጠል ውይይቶችን እያደረጉ ይገኛሉ።

በስብሰባው የሚደርሱበትን ውጤትም የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት አባል ሀገራት የፖሊስ መሪዎች ጠቅላላ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ አቅርበው ልዩ ልዩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ተገልጿል፡፡

በጋራ ስብሰባው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ አዛዥና የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ቋሚ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ÷ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ተቀናጅቶ ለመከላከል እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዚህም አባል ሀገራት ተሞክሮአቸውን በማካፈል እና ለሚስተዋሉ ችግሮች የጋራ መፍተሄ በማስቀመጥ ውስጥ ሁሉም የኮሚቴ አባላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.