Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ የኑሮ ውድነት የሴት ተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ እንዲጨምር ማድረጉ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ የሴት ተማሪዎች ትምህርት የማቋረጥ ምጣኔው እንዲያሻቅብ ማድረጉን ‘ካምፌድ አፍሪካ’ አስታወቀ፡፡

በአህጉሪቱ ያለው አነስተኛ ክፍያ፣ ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲሁም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሴቶች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ እያደረገ ስለመሆኑም ነው የተገለፀው፡፡

በሴት ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎ እና ድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረቱን ያደረገው ካምፌድ አፍሪካ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንዳስታወቀው÷ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እዲንሁም የምግብና ነዳጅ ወጪ መጨመር ባለፉት 18 ወራት በርካታ ሴት ተማሪዎች ትምህርት እንዲያቋርጡ ምክንያት ሆኗል፡፡

እነዚህ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ጫናዎች የታዳጊ ሴቶችን የመማር እድል እያመከኑ ነው ያለው ድርጅቱ÷ በስድስት ዓመታት ውስጥ 6 ሚሊዮን ታዳጊ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ አቅዶ እየሰራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

እቅዱን ለመፈጸምም 414 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ እና ለዚህም መንግስታትና ለጋሽ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ድርጀቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ዩኒሴፍን ጠቅሶ ዘጋርዲያን እንደዘገበው፤ በዓለም 129 ሚሊየን ልጃገረዶች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ ሲሆኑ ከነዚህም መካከል 32 ሚሊየን የሚሆኑት የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሁም 97 ሚሊየን የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.