እስራኤል ወደ ጋዛ እግረኛ ተዋጊ የማስገባት እቅዷን እንዳራዘመች አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2016፣ (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል ወደ ጋዛ የእግረኛ ጦር ለማስገባት ያወጣችውን እቅድ ማራዘሟን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋዛ የምድር ዘመቻ ለማድረግ በወጣው እቅድ ላይ አለመፈረማቸውን ተከትሎ ከጦራቸው ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተዋል የተባለ ሲሆን ኔታኒያሁ ውሳኔያቸውን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጠይቀዋል፡፡
የእስራኤል ጦር አመራሮች ለሃማስ አፀፋ ከመስጠት በተጨማሪ ቡድኑን ለማጥፋት ቢስማሙም ሃማስን ለማጥፋት በሚደረጉ የጦር ስልቶች ላይ ግን መግባባት ላይ እንዳልደረሱ ምንጮችን ጠቅሶ አር ቲ ዘግቧል፡፡
እስራኤልከ ከሃማስ ጥቃት በኋላ 360 ሺህ የሚጠጉ ተጠባባቂ ወታደሮችን ያሰባሰበች ሲሆን ለሶስት ሳምንታት በተመረጡ የሃማስ ኢላማዎች ላይ የአየር ድብደባ ስታደርግ ቆታለች፡፡
እስካሁን እግረኛ ተዋጊ ወደ ጋዛ ሰርጥ ባይገባም በተወሰኑ የፍልስጤም ግዛቶች መጠነኛ የምድር ተዋጊ ወታደሮች እንቅስቃሴ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ቀደም ሲል ዋሽንግተንና የተወሰኑ የአውሮፓ አጋር ሀገራት ቴል አቪቭ በምድር ላይ አካሂደዋለሁ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ እንድታዘገየው ጫና ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡