የደቡብ ኮሪያዋ ቾንቹን ከተማ ከንቲባ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ እህት ከተማ የሆነችው የደቡብ ኮሪያዋ ቾንቹን ከተማ ከንቲባ ዩክ ዶንግ ሃን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ከልዑካን ቡድናቸው ጋር አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ከንቲባ ዩክ ዶንግ ሃን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ከንቲባ ዩክ ዶንግ ሃን የሁለቱ እህትማማች ከተሞች የ20ኛ ዓመት ክብረ በዓል የሚያከብሩ ሲሆን የሁለቱን ከተሞች ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር እንደሚመክሩ የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
የልዑካን ቡድኑ በቆይታው ለአብርሆት ቤተ-መፅሃፍት መፅሃፍት ማበርከትን ጨምሮ በከተማዋ የተገነቡ ታላላቅ ፕሮጀክቶችንና ትምህርት ቤቶችን እንደሚጎበኙ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም የሁለቱን ከተሞች የባህል ልውውጥ ፌስቲቫል በማድረግ ከኮሪያ ዘማች አርበኞች ጋርም ልዑካን ቡድኑ ቆይታ ያደርጋል ተብሏል፡፡