Fana: At a Speed of Life!

ኤልኒኖ ባስከተለው ድርቅ በፓናማ ቦይ የመርከቦች ቁጥር ሊቀነስ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፓናማ ቦይ በ70 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ በመመታቱ ምክንያት መተላለፊያውን የሚጠቀሙ መርከቦችን ቁጥር የበለጠ እንደሚቀንስ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የፓናማ ቦይ አስተዳደር ከፈረንጆቹ 1950 ጀምሮ በጥቅምት ወር ታይቶ የማይታወቅ ደረቃማ ሁኔታ በመመዝገቡ ውሳኔውን ለመወሰን መገደዱን ተናግሯል።

የኤልኒኖ የአየር ሁኔታ ክስተት ለከባድ ድርቅ አስተዋጽኦ ማድረጉም ተገልጿል።

ውሳኔውም በዓለም ዙሪያ ሸቀጦችን የማጓጓዣ ወጪ ላይ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል።

መርከቦች በአትላንቲክ እና በፓሲፊክ ውቅያኖሶች መካከል የሚጓዙበትን ጊዜ እና ርቀት በእጅጉ የሚቀንሰው የፓናማ ቦይ፤ በቀን ለ24 ሰዓታት፣ በዓመት ለ365 ቀናት አገልግሎት ይሰጣል።

መስመሩ በዓመት ከ13 ሺህ እስከ 14 ሺህ መርከቦች እንደሚስተናገዱበት አስተዳደሩ ገልጿል።

በጋቱን ሀይቅ ውስጥ ያለው እና በዝናብ ላይ በተመሰረተ ለመተላለፊያው ጥቅም ላይ የሚውለው ዋና የውሃ ማጠራቀሚያ፣ በዚህ ዓመት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የውሃ መጠኑ ማሽቆልቆሉንም አመላክቷል።

ከፈረንጆቹ ህዳር 3 ጀምሮም በቀን የሚያስተናግዳቸውን 31 መርከቦች ቁጥር ወደ 25 እንደሚቀንስ ያመለከተው ባለስልጣኑ፤ ከየካቲት 2024 ጀምሮ ደግሞ በቀን 18 መርከቦችን ወደ ማስተናገድ ሊገባ እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.