Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ ያመጠቀቻቸው ሳተላይቶች ተልዕኳቸውን በስኬት ማጠናቀቃቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ ያመጠቀቻቸው ሳተላይቶች ተልዕኳቸውን በስኬት ማጠናቃቸውን የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢትዮጵያ ETRSS-02 የሚል ስያሜ የተሰጣትን ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በሁለት ዓመታት ውስጥ ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ መሆኗንም ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ፤ ሶስተኛውን ሳተላይት መምጠቅን በተመለከተ መንግስት የፋይናንስና የኢኮኖሚ አዋጪነት ጥናት ማድረጉን ገልጸዋል።

ጥናቱ ከዚህ በፊት ወደ ሕዋ ከመጠቁት ሳተላይቶች ተሞክሮ በመውሰድ የቀጣዩን ሳተላይት መረጃ ከመጠቀም አልፎ ሌሎች ተልዕኮዎችን በግልጽ ማስቀመጡንም አመልክተዋል።

የሳተላይቱን ጨረታ የተመለከተ መረጃ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዢ ስርዓት ውስጥ እንዲገባ መደረጉንና በቀጣይ ወራት ዓለም አቀፍ ጨረታ እንደሚወጣም ተናግረዋል።

በታህሳስ 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን ETRSS-01 የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ሕዋ መላኳ ይታወሳል።

በታህሳስ 2013 ዓ.ም ደግሞ ET-Smart-RSS የተሰኘችውን ሁለተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በተመሳሳይ ከቻይና ወደ ሕዋ አምጥቃለች።

የመጀመሪያዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት በሕዋ ከሁለት ዓመት ከግማሽ እስከ ሶስት ዓመት እንዲሁም ሁለተኛው ሳተላይት ደግሞ ቢያንስ ለአንድ ዓመት እንደምትቆይ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

በዚሁ መሰረት ሳተላይቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ የአገልግሎት ጊዜያቸውን አጠናቀው የተሰጣቸውን ተልዕኮ ማሳካታቸውን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።

ETRSS-01 የተሰኘችው ሳተላይት ከተቀመጠላት ጊዜ በላይ ተጨማሪ ዘጠኝ ወራት አገልግሎት መስጠቷን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በቀጣይ ሳተላይቶቹን ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የማስወገድ ስራ እንደሚከናወንም አመልክተዋል።

ከሳተላይቶቹ የተገኙት መረጃዎች ለግብርና፣ ቱሪዝም፣ መሬት አስተዳደር፣ ተፈጥሮ ሀብት፣ ለአደጋ ስጋት ቅነሳና ሌሎች ስራዎች በግብአትነት መዋላቸውን አመልክተዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.